30/08/2026
ከሆላንድ የመጡ እንግዶች በኮንሶ ዞን የማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም እንቅስቃሴዎችን ጎበኙ፣
ካራት፣ ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም (ኮንሶ ዞን ኮሙኒኬሽን)
ከሆላንድ የመጡ በአፍሪካ የማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም (Community-Based Tourism) ፕሮግራም ማናጀርና ደጋፊዎች፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከከተማ የቱሪዝም ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችና አመራሮች በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችንና የቱሪዝም ሀብቶችን ጎበኙ።
ጎብኚዎቹ ካራት ከተማ ሲደርሱ በኮንሶ ዞን ዋና አስተዳደር ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ደመላሽ ጎንዲሼ፣ የካራት ከተማ አስ/ር ከንቲባን ጨምሮ የከተማው አመራሮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
አቀባበሉን ተከትሎም ወደ ጋሞሌ አምባ መንደር በመጓዝ በፕሮግራሙ የተካተቱ የቱሪዝም ምርቶችን፣ የአካባቢውን ባህላዊ ሀብቶችና የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማሳያ ደረጃ ተመልክተዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ፕሮግራሙ በኮንሶ ዞን ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በመለየት፣ በማደራጀትና ለቱሪስት ገበያ በተስማሚ መልኩ በማቅረብ ማህበረሰቡ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በቀጥታ እንዲያገኝ ያለመ ነው።
በካራት ከተማ ባህልና ስፖርት ጽ/ቤት የቱሪዝም ባለሙያ አቶ ኦላታ ኦርካይዶ እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት በፕሮግራሙ የቅድመ ሁኔታ መረጃ የማሰባሰብና የማፒንግ ሥራዎች ተከናውነዋል።
አቶ ኦላታ ጨምረው ከማህበረሰቡ ጋር የተፈጠረው ቀጥተኛ መግባባትና ጎብኚዎችን በፈገግታ መቀበል የኮንሶ የቱሪዝም ሀብት አካል የሆነውን የእንግዳ ተቀባይነት በግልጽ ያሳያል ብለዋል።
በዚህም በጋሞሌ አምባ መንደር፣ በካራት ከተማና በኮንሶ ዞን ለቱሪስት ገበያ ሊቀርቡ የሚችሉ የቱሪዝም ምርቶችና እንቅስቃሴዎች ተለይተው በአጭር ፓኬጅ መልክ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የተዘጋጁት መረጃዎች በክልሉ በኩል ለፌዴራል የቱሪዝም ሚኒስቴር መቅረባቸውን ጠቁመው፣ የዛሬው ጉብኝት ዋና ዓላማ በሰነድ የተዘጋጁት የቱሪዝም ምርቶች በመሬት ላይ በተግባር መኖራቸውን ማረጋገጥ፣ ያሉ ክፍተቶችን መለየትና ለቀጣይ ትግበራ መነሻ የሚሆኑ ምልከታዎችን ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ቱሪስቶች መጥተው አንድን ቦታ ብቻ ጎብኝተው ከመሄድ ይልቅ በአካባቢው ቆይታ እንዲያደርጉ፣ ከማህበረሰቡ ጋር በቀጥታ እንዲገናኙና የአካባቢውን ባህል፣ ምግብ፣ መጠጥና እደ ጥበብ በተግባር እንዲያውቁ የሚያስችል መሆኑንም አቶ መላሽ ገልጸዋል።
እንደ «ዋካ» ያሉ የኮንሶ ባህላዊ ሀብቶችን በመመልከት ብቻ ሳይሆን አጠራሩንና አሠራሩን በተግባር በመሳተፍ እንዲረዱ ማድረግ ቱሪስቶችን በአካባቢው ለማቆየትና የቱሪዝም ገቢው በአካባቢው እንዲዘዋወር ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ መልኩ የቱሪዝም ጥቅም ለአካባቢው ማህበረሰብ፣ በእደ ጥበብ ለተሰማሩ ወገኖችና ከቱሪዝም ጋር በተያያዙ ሥራዎች ለሚሳተፉ ግለሰቦች እንዲደርስ በማድረግ የካራት ከተማንና የዞኑን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን አቶ መላሽ አስረድተዋል።
በጉብኝቱ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ተወካዮች፣ የኮንሶ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፣ የካራት ከተማ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ፕሮግራሙን በፋይናንስ ከሚደግፉ አጋሮች መካከልም ከሆላንድ የመጡት እንግዶች መሆናቸው ተገልጿል።
በጋሞሌ አምባ መንደር የተደረገው አቀባበል የኮንሶን ባህላዊ እንግዳ ተቀባይነትና የማህበረሰቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያሳየ ሲሆን፣ የአካባቢው ሽማግሌዎችና ማህበረሰቡ እንግዶቹን በፈገግታና በቅርበት መቀበላቸው ለጎብኚዎቹ ልዩ ልምድ ፈጥሯል።
ከሆላንድ የመጡት የCBT-CBI ፕሮግራም ማናጀር ዣኔት (Jeanette) በጉብኝቱ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውንና ኮንሶ በርካታና የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የያዘ መሆኑን ከጉብኝታቸው መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ፕሮግራሙ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ የዛሬው ጉብኝት በቀጣይ በጋራ ሊከናወኑ ለሚገባቸው ሥራዎች ጠንካራ መነሻ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ማጠናቀቂያም የከርቲታ ጎሳ መሪ ካላ ገዛኼኝ በሚገኙበት ባህላዊ ቤት በመገኘት የኮንሶን ባህላዊ አኗኗር፣ የአካባቢውን የቱሪዝም ሀብትና ባህላዊ ልምዶች ተመልክተዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊዎችም በቀጣይ ሊተገበሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በቅንጅትና በጋራ መሥራት፣ የቱሪዝም ምርቶቹን በተግባር ማጠናከርና ማህበረሰቡ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም እንዲያሳድግ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
የኮንሶ ዞን የማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም እንቅስቃሴም ከቅድመ ዝግጅትና ምልከታ ወደ ተግባራዊ አፈጻጸም በመሸጋገር የአካባቢውን ባህልና ቱሪዝም ሀብት በመጠቀም ለማህበረሰቡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚፈጥር ሥራ እንደሚሆን ተገልጿል።