18/08/2026
የአሸንድዬ በዓልን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች ተከናውነዋል።
ቅዱስ ላሊበላ፦ነሐሴ፣12፣2018(ቅዱስ ላሊበላ ኮሙኒኬሽን) የአሸንድዬ በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች የገለፁት።
አሸንድዬ ክረምቱ ሊገባደድ ሲቃረብ ከወርሐ ነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በላስታ ላሊበላ አካባቢዎች በውብ ልጃገረዶች ጨዋታ ደምቆ የሚከበር በዓል ነው ።
በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 20 ባሉት ቀናት ሴቶች አምረውና ተውበው በቡድን በቡድን በመሆን ከአብያተ ክርስቲያናት በመጀመር በየሰፈሩ እየዞሩ የበዓሉን አከባበር ትዕይንት የሚያሳዩበት ነው።
ደረቃማው ምድር አረንጓዴ ለብሶ፣ሳር ቅጠሉ አብቦ፣ የደፈረሱ ወንዞች ጠርተው፣ሰማይ ብሩህ ሲሆን ወጣት ሴቶች እና ወንዶች አምሮባቸው አደባባይ ይወጣሉ።
በዓሉን ለማክበር ሴቶች፣በአካባቢው ባህል አለባበስ፣ አጊያጊያጥ ተውበው፣ፀጉራቸውን ሳዱላና ሹሩባ ተሰርተው ሲዘጋጁ፣ሴቶቹን የሚያጅቡት ወንዶች ደግሞ ንጹህ ለብሰው ጅራፋቸውን የሚያዘጋጁበት ወቅት ነው።
ከተማ አስተዳደሩ ከከተማው ሴቶች ጋር የአሸንድዬ በዓል አከባበር ዝግጅት ላይ ያተኮረ ውይይት አደርጓል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ደስታ ጓንቸ ፦ አሸንድዬ ለሴቶች ልዩ በዓል ነው መሆኑን ነው የገለፁት።
ከአያት ቅድመ አያት ሲተላለፍ የመጣውን ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት በተራቸው ጠብቀው ለትውልድ ለማስተላለፍ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ አስታጥቂው ቢሰጥ በበኩሏ
ሁሌም አሸንድዬን በድምቀት የሚያከብሩት በዓል መሆኑን በመጥቀስ ዘንድሮም በዓሉን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ነው የገለፀችው።
ባህሉን ማጠናከርና ለቀጣይ ትውልድ ሳይበረዝ ለማስተላለፍም የድርሻቸውን እየተወጡ ስለመሆኑ ነው የከተማዋ ነዋሪዎች ያመለከቱት።
አሸንድዬ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቱ ሳይበረዝ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግእየተሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የቅዱስ ላሊበላ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊዋ ዮርዳኖስ መርሻ ናቸው።
በዓሉን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም ነው ያነሱት ።
በየአካባቢው የአሸንድዬ አጨዋወትን የሚያሳዩ የልጃ ገረዶች፣የወጣቶች ዝግጅት፣የአካባቢው የአመጋገብ ስርዓትና ሌሎችም የበዓሉ አካል የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም ተመላክቷል።
በዓሉ ከነሐሴ13 ጀምሮ የሚከበር ሲሆን ወጣቶች ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያሳዩበት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ባህሉን መሰረት ያደረጉ ፅሁፎችም ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ነው የተመላከተው።
የቅዱስ ላሊበላ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናት ወጣቶች ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ሃላፊዋ ሰርኬ መኳንንት በበኩላቸው የአሸንድዬን ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቱን ለመጠቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ልጃ ገረዶች፣እናቶች፣ ከአለባበስ ጀምሮ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የጠቀሱት።
ትውፊቱን ጠብቆ ለማቆየት ሴቶች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።