02/03/2026
I think this is the fact history.
የዓድዋዉ ምንሊክ...!
ከዓድዋ በፊት በየአካባቢው ያሉትን ሹሞች እና ሕዝቦች ማስገበር ነበረበት። በመላም በዱላም ያንን አደረገ። ያንን ባደረገ ማግስት ነጭ ወራሪ መጣ። ምንሊክ ለእርምጃ አልተጣደፈም። ተቻኩሎ ሳይፍ አልመዘዘም። ደካማ መስሎ ቀን ጠበቀ። ጦርነትን መጀመር ያለብህ እንደምታሸንፍ እርግጠኛ ስትሆን ነው የሚለውን መርሕ በልቡ አኖረ። በዲፕሎማሲ ጉዳዩን ለመፍታት ጣረ። ወደብ ላይ በጣሊያን መንግስት ተይዞ የታገቱበትን ሁለት ሚሊየን ጥይት አስለቀቀ። ወደ ሞስኮ መልዕክተኞችን ልኮ ከንጉስ ኒኮላይ በ10 ሺህ የሚቆጠር ጠብመንጃ አገኘ።
በወቅቱ ለጣሊያን ያደረውን የዋጉን ዋቅሹም ብሩን አስሮ የዋግ ሹምነትን ለዋቅሹም ልጅ ሰጠ። ከትግራይ ከጣሊያን ጋር ለመተባበር ሲሰሩ የነበሩትን ራስ መንገሻንም ከጣሊያን ጋር አጋጭቶ እንዲዋጉ አደረገ። ራስ መንገሻ በጣሊያን ከተሸነፉ በኃላ አሉላ አባነጋን ይዞ ወደ አዲሳባ መጥቶ ይቅርታ ጠየቁ። ምኒልክ እዚህም ጋ ጥበብ የተሞላበት ስልት ተጠቀሙ። ወደ ግዞት አልላካቸዉም። አስሮ አላሰቃያቸዉም። የነገዉን ትልቁን ምስል ተመለከተና ሹሞ ሸልሞ ሸኛቸዉ።
የቁርጡ ቀን ደረሰ። የክተት አዋጅ ታወጀ። የክተት አዋጁ በዓለም ላይ አጭሩ የጦርነት ጥሪ ነው። ያልተንዛዛ ፣ እጥር ምጥን ያለ የክተት አዋጅ ነው። የት፣መቼ፣ እንዴት...የሚሉትን ጥያቄዎች የመለሰ የማያሻማ ግልፅ አዋጅ ነው። አዋጁ ዛሬም ድረስ ትልልቅ የጦርነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጭምር የማስተማሪያ ሰነድ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ሕዝቡም የተባለውን አደረገ። ቀንበሩን ሰቅሎ፣ ስንቁን ቋጥሮ ወደ ወረ ኢሉ ተመመ። ከዛ ወዲህ ያለው ታሪክ ነው። የመሪ ጥበብ፣ ቀናኢ ሕዝብ፣ ልባም አዋጊ፣ ሞትን የናቀ ተዋጊ ባንድ ልብ አድሮ ባንድ ልብ ተፋለሙ።
አይደፈሬ የተባለው የአምባላጌዉ ምሽግ በገበየሁ ተሰበረ። የመቀሌው እንዳየሱስ ጦርነት በጣይቱ ስልትና ብልሐት ወራሪው ተረታ። በዓድዋ'ም የበሻ አውአሎም የስለላ ጥበብ፣ የአሉላ ጀግንነት፣ የባልቻ ገድል፣ የራስ መኮንን ፈረሰኞች አይበገሬነት ተጣምሮ በዓለም ታሪክ አዲስ ትርክት አኖሩ። ያቺን የነፃነት ሰንደቅ በዓድዋ ተራራ ላይ ሰቀሉ። ጥቁር ነጭን ረታ! በቃ ይህ የገድሎች ሁሉ ገድል የድሎች ሁሉ ድል ሆነ...
ከዚህ ሁሉ ድል ጀርባ ግን ያ ንጉስ አለ!
(ጥላሁን ያሚ)