02/09/2026
የጉራፈረዳ ወረዳ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን ገመገመ
የጉራፈረዳ ወረዳ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም የ2018 በጀት ዓመት የተግባራትና የካፒታል በጀት አፈጻጸም የፌደራል እና የክልል አካላት በተገኙበት ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የጉራፈረዳ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስጌን ጨምዴሳ እንደገለፁት በወረዳችን ሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም የማህበረሰቡን ችግር ከመቀነስም ባለፈ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አልሞ እየሰራ ያለ መሆኑን ጠቅሰዉ ፕሮግራሙ ትኩረት ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰራ በመሆኑ በ2019 የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል።
በመድረኩ የሰቆጣ ቃል ኪደን ፕሮግራም በጤና፣ በግብርና፣ በሴቶችና ህጻናት ፣ በውሃ ፣ በእንስሳትና በሌሎችም ዘርፍ በ2018 በጀት ዓመት የተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት የጉራፈረዳ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የእናቶችና የህፃናት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታሪኩ ተስፋዬ በዝርዝር አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ከፌደራል ጤና ሚኒስተር እና ከክልል ጤና ቢሮ የመጡ ባለድርሻ አካላት እንደገለፁት በወረዳው በሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም በጀት ዓመት የተከናወኑ የልማት ስራዎች መሬት ላይ የሚታዩ፣በጥራትና በፍጥነት የተከወኑ መሆናቸው የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው ቀጣይ ዘላቂ ሃብት እንዲሆኑ ተቋማት ኃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል::
ለሰቆጣ ፕሮግራም የተበጀተን በጀት ለታለመለት አላማ በማዋል ተግባራትን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በመቀናጀትና በመናበብ መስራት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የፕሮግራሙ አላማ ለማሳካት እየተሰሩ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫና የካፒታል ስራዎች አቀናጅተን በመምራት በአዕምሮና በአካል የዳበረ ትውልድ መፍጠር የሁላችንም ተግባርና ኃላፊነት በመሆኑ ለቀጣይ ለ2019 በጀት አመት ለበለጠ ውጤት እንሰራለን በማለት የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።