01/09/2026
የሃይማኖት ተቋማት የሕብረተሰቡን የሞራል ልዕልና እና የጋራ አብሮነትን ጠብቆ ለማቆየት ያላቸውን ሚና ማጠናከር አለባቸው -ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
የሃይማኖት ተቋማት የሕብረተሰቡን የሞራል ልዕልና፣ የሰላም እሴቶች እና የጋራ አብሮነትን ጠብቆ ለማቆየት ያላቸውን ሚና አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልና 18ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ወቅት ጉባኤው አያሌ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የሕዝቦቿ አብሮነት እና የጋራ መሻታችን የምንዘክርበትና የምንመክርበት ታሪካዊ መድረክ ነው ብለዋል።
ጉባዔው ላለፉት 15 ዓመታት የእምነት ተቋማት በትብብር እና በኅብረት ለኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ ከፍ ያለ ፋይዳ እና መሠረት ያለው መሆኑን ያስመሰከሩበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የማስተዋል እና የአብሮነት መገለጫ ይሰምር ዘንድ 15 ዓመታትን መሻገሩ ጉባዔውን ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ተከታታይ ትውልዶች በሐሳባቸው፣በጉልበታቸው እና በጸሎታቸው የገነቧት ታላቅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መሠረት ለእምነታችን ያለን ጽናት፣ ለሰው ልጅ ያለን ከበሬታ እና ለብዙኅነታችንና አንድነታችን የምንሰጠው ከፍ ያለ አክብሮት ነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ምሰሶዎች እና ማገሮች መካከል ደግሞ ለዘመናት የሕዝቡን ሞራልና ስብዕና ሲቀርጹ የኖሩት የእምነት ተቋማት መሆናቸውን አመልክተዋል።
የሃይማኖት አባቶች የሕዝቡ የሞራልና የሥነ-ምግባር ዋና ጠባቂ መሆናቸውን ገልጸው፤ በተለይም ታዳጊዎች እና ወጣቶች በውጭ የተውሶ ሐሳቦችና ደራሽ ወጎች እንዳይወሰዱ ትምህርት መለገስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና የሕዝቧ ጽናት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲታነጽ ከፍ ያለ ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አልፎ አልፎ ከኢትዮጵያዊ ባህል፣ ሥነ-ምግባር፣ ሕሊና እና ጨዋነት ውጭ የሆኑ ቅጥፈት፣ እብለት፣ ሌብነት፣ ውስልትና፣ ጭካኔ እና ለሰው ልጅ ሕይወት ደንታ ቢስነት ጎልተው እንዳይታዩ በርትቶ መከላከል እና ማስተማር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚህ የጥፋት መንገድ የሚመላለሱትን በመገሰጽ፣ ስሜታቸውን ተቆጣጥረው ይሄዱ ዘንድ ማረም እና የሚበጁ ዜጎችን ማውጣት ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።
የእምነት መሪዎች በጨለማ ውስጥ ብርሃንን የሚፈነጥቁ መቅረዞች፣ በተስፋ መቁረጥ ማዕበል ውስጥ እንደ ጽኑ አለት የቆሙ የብርታት ምንጮች እና በተከፋፈሉ ልቦች ውስጥ የመመካከር፣ የመተባበር፣ የይቅርታ እና የእርቅ "ሐዋርያት" እና "ሱሃቦች" ናችሁ ብለዋል።
በተለያዩ መድረኮች ለዘመናት የገነባነው መተሳሰብ፣ መደጋፍ እና መከባበር ለመናድ የሚታትሩ እንዲሁም መከፋፈልን እንደ ታላቅ ስኬት የሚቆጥሩ ድምጾች የተበራከቱበት ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ ባካሄደችው ሀገራዊ የምክክር መድረክ የእምነት ተወካዮች ድርሻ ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ ከፍ ያለ እንደነበር መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶች የሂደቱ ተሳታፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሀገራዊ ስክነትን ለመላበስ በሚደረገው ጥረት ሁሉ የላቀ ሚና እንደነበራቸው ተናግረዋል።
መመካከር በእውነት፣ በይቅር ባይነት እና በጋራ መግባባት ላይ እንዲጸና፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሐሳቡን እንዲያጋራ፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና እድገት መሠረት ይጣል ዘንድ ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣታቸውን አንስተዋል።
ሀገራዊ ዕድገትና ልማትን ማገዝ እንዲሁም በንቃት መሳተፍ የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን ገልጸው፤ ከዘመኑ ዓለም አቀፋዊ ዕድገት ጋር እኩል መራመድ እና እድገትን ማላቅ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
መንግሥት የእምነት ተቋማት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ለማህበራዊ ውህደትና ለአጠቃላይ ዕድገት የሚያደርጉትን ላቅ ያለ አስተዋጽኦ በጥልቅ እንደሚረዳ እና የጎላ እውቅናና ከበሬታ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
(ኢዜአ
በሚከተለዉ የሚዲያ አማራጮች ይከታተሉን
📌Tiktok
tiktok.com/
📌Telegram
https://t.me/benchshekozonecommunication
📌 Youtube
https://youtube.com/?si=PUe2-AlSQHCpY1_r
📌 WhatsApp
https://chat.whatsapp.com/IDBp91eytBbL0m0u2rSiSU