27/08/2026
በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው 17 የቤተሰብ አባላት ድጋፍ ተደረገ
---------------------------
ሰንበቴ: ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም(ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ጤና ፅ/ቤት)
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የ2018 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ምክንያት በማድረግ በሉጎ ቀበሌ በሦስት አባዎራዎች ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እና የገንዘብ ድጋፍ በዛሬው እለት አድርጓል።
በደረሰው የእሳት አደጋ የሶስት አባወራዎች መኖሪያ ቤት ንብረታቸውን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን በጠቅላላው 17 የቤተሰብ አባላት ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው ተገልጿል።የደረሰውን አደጋ ተከትሎ የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በቦታው በመገኘት አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ አድርገዋል።
ጽ/ቤቱ በወረዳው የሚገኙ አራት ጤና ጣቢያዎችን በማስተባበር ለምግብነት የሚውሉ ሩዝ፣ ዱቄት እና ዘይት እንዲሁም የህፃናት እና የአዋቂዎች አልባሳት፣ የንጾህና መጠበቂያ የልብስ እና የገላ ሳሙናዎች፣ የውኃ ጀሪካኖች እና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ነው ያደረገው።ከዚህ በተጨማሪም ተጎጂዎቹ በሉጎ ጤና ጣቢያ ሙሉ ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማመቻቸቱንም ጽ/ቤቱ ገልጿል።
የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ኡመር በድጋፍ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ዛሬ እዚህ የተገኘነው ለቁሳቁስ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ከጎናችሁ መሆናችንን ለመግለጽ ነው በማለት ተናግረዋል።በቀጣይም እንደ ወረዳ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
በእሳት አደጋው ጉዳት የደረሰባቸው የቤተሰብ ተወካይ በበኩላቸው በደረሰባቸው ድገተኛ አደጋ መጠለያ እና ንብረታቸውን አጥተው በተጨነቁበት ሰዓት ጤና ጽ/ቤት ባደረገላቸው የቁሳቁስ፣ የገንዘብ እና የነፃ ሕክምና ድጋፍ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለጽ ከጎናችን ስለቆማችሁ እናመሰግናለን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዚሁ የድጋፍ መርሃ-ግብር ላይ የጽ/ቤቱን ኃላፊ አቶ አህመድ ኡመርን ጨምሮ የጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አፍራህ ሰይድ፣ የጽ/ቤቱ ኦፊሰሮች እና የአራቱም ጤና ጣቢያ ተወካዮች በቦታው በአካል ተገኝተው ለተጎጅዎች ድጋፉን አበርክተዋል።
መረጃ:ከጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ጤና ፅ/ቤት ከሚድያ ክፍል የተገኘ