04/08/2026
"ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የዜጎች ጤናን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል"- አቶ እንዳሻው ሽብሩ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የ 2018 በጀት ዓመት የጤና ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ አፈፃፀም መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
በበጀት ዓመቱ የእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር፣ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትና ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም ነባርና አዳዲስ ወረርሽኞችን መከላከል ላይ የተሰራዉ ስራ አበረታች መሆኑ ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በመዋቅሮች መካከል የሚስተዋለውን የአፈፃፀም ልዩነት ማቀራረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በክልሉ በሚከናወኑ የጤና ልማት ስራዎች ሕብረተሰቡን ባለቤትና ተሳታፊ ማድረግ ይገባል ያሉት ኃላፊው ለአብነትም 83 የማህበረሰብ ፋርማሲዎችን በሕብረተሰቡና በአጋር አካላት ትብብር ብቻ መገንባት እንደተቻለ ጠቁመዋል።
በክልሉ 43 ወረዳዎች የሰቆጣ ስምምነትን ተግባራዊ በማድረግ የህፃነት መቀንጨርና የስርዓተ- ምግብ ችግሮችን ለመፍታት በመሠራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ከማህበረሰብ የጤና መድህን እና ከህፃናት መቀንጨር ችግሮች ጋር በማስተሳሰር ለመፍትሄዉ መስራት ይገባል ብለዋል።
ጤናማ ህብረተሰብ ሳይኖር ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም ያሉት ኃላፊዉ ለሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ የዜጎችን ጤና ማስጠበቅ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ 1.39 ሚሊዮን ሴቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንዲያገኙ በቅንጅት መሠራቱ ተመልክቷል።
በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ጠቅላላ ሽፋን 1.01 ሚሊዮን በላይ ማድረስ እንደተቻለም አስረድተዋል።
በሕብረተሰብ ጤና ላይ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ነባርና አዳዲስ በሽታዎች፤ ወረርሽኝ እና የተፈጥሮ አደጋ ክስተቶችን አስቀድሞ በመለየትና ምላሽ የመስጠት አቅም መገንባት ተችሏል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የክልሉ ጤና ቢሮ ላከናወናቸው አመርቂ ስራዎች ዕዉቅና መስጠት እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል።
ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ መስራት፣ ግንባታቸዉ የተጓተቱ የጤና ተቋማትን ማጠናቀቅ፣ የህፃናት መቀንጨርና የስርዓተ ምግብ ችግሮች ላይ ከታች ጀምሮ መስራት፣ የወባ ስርጭትና መከላከል ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ የክልሉ ጤና ቢሮ የ 2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ዉይይት በማድረግ የጋራ ተደርጓል።
በመድረኩ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የክልሉ ጤና ቢሮ የማኔጅመንት አባላት፣ የጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።