30/12/2021
የትህነግ አክቲቪስቱ ልደቱ
በ2002 ዓ/ም ይመስለኛል። አንድ ዩኒቨርሲቲ የምናውቀው የልደቱ ፓርቲ አባል ልደቱን ስንተቸው ሰምቶ "ኑ እስኪ ስብሰባ ታዘቡ ልውሰዳችሁ" ይለናል። አንድ እሁድ ሄድን። የፓርቲ ሰዎቻቸው ውይይት ነበር። ጥያቄ የሚጠይቁ በእድሜ ገፋ ያሉም ወጣቶችም አሉ። ልደቱ እነሱን ተቃርኖ በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረውን ትህነግ/ኢህአዴግ ያንቆለጳጵሳል። መጀመርያ ከምንተቸው በላይ የከፋ አቋም እንዳለው ተረዳሁ። ኢህአዴግኮ ይህን ያህል ልማት ያመጣ ነው፣ ይህን ያህል መንገድ ሰርቷል እያለ የፓርቲውን አመራርና አባላት ሊሞግታቸው ይሞክራል። በወቅቱ ትህነግ/ኢህአዴግ በሚኒስትር ድኤታ ደረጃ ወደ ስብሰባው ወኪል ቢልክ ከዚህ የበለጠ የሚከራከራቸው አይመስለኝም።
ተጋብዘው የመጡ ናቸው ተብለን ለእኛም እድል ሰጡን። "አንተ ለኢህአዴግ የምትሰራ ሲቪክ ተቋም ነህ፣ አክቲቪስት ነህ?" ብዬ ጠየኩት። ጭፍን ተቃዋሚ አይደለንም፣ ሌላ ጊዜ ስላልመጣህ ይሆናል እንጅ እንወቅሳቸዋለን ወዘተ ብሎ መለሰልኝ። ድሮም ልደቱ የትህነግ አክቲቪስት ነው። አሁንም እንደዛው።
ከታች ያለውን ቪዲዮ ተመልከቱት። ኢትዮጵያውያን ለምን አንድ ህወሃት የሚባል ድርጅትን እንዲህ ይጠላሉ ይለናል። አንድ ህወሃት የሚለው ቡድን በጥላቻ ማንፌስቶ ሕዝብን አጠፋለሁ ብሎ የተነሳው። ለምን ትጠሉታላችሁ የሚለው ቡድን ነውኮ ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ የመጣው። ንፁሃንን የጨፈጨፈው። ሴቶችን የደፈረው። ሀብትና ንብረት ያወደመው። ልደቱ የተወለደው ላስታ ነው። ላስታ በትህነግ ወድሟል። ይህን የልደቱን ንግግር ወገኖቻቸው የተጨፈጨፈባቸው የላስታ ሰዎች ቢሰሙት ምን ይሉ ይሆን?
ልደቱ ትህነግ ለምን ሌሎቹን ይጠላል ብሎ ጠይቆ አያውቅም። አይወቅስምም። በጥላቻ ሕዝብን ካላጠፋሁ የሚለውን የትግሬ ወራሪ አይተችም። የተበደለውን ሕዝብ ግን ለምን ህወሃትን ትጠሉታላችሁ ብሎ ይወቅሳቸዋል። የውጭ ጠላት ይዞ የመጣውን የትግሬ ወራሪ አይተችም። ኢትዮጵያውያንን ግን የትግሬ ወራሪን ብቻ ሳይሆን ትግሬን ትጠላላችሁ እያለ ይተቻል። ከእርጉዝ እስከ ህፃን፣ ከሽማግሌ እስከ 13 አመት ልጅ ተደራጅቶ ሲወርር አንድ ቀን ተችቶ አያውቅም። ልደቱ ከመጀመርያው ጀምሮ የትግሬ ወራሪ አክቲቪስት ነው! by ጌታቸው ሺፈራው