14/04/2026
አመራሩ ፈተናዎችን በማሸነፍ፣ የፓርቲና የመንግሥት ተልዕኮዎችን በትጋት በመፈጸም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መሥራት አለበት፦ አቶ ዳዊት ወንድሙ
በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ እና ዋካ ከተማ አስተዳደር የመራጮች ምዝገባ አፈጻጸም፣ የመንግስት መደበኛና ወቅታዊ ተግባራት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የውይይትና ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩን በጋራ ያስጀመሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ም/ኃላፊና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት ወንድሙ እና የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አክልሉ ለማ ናቸው።
በመድረኩ ዋና ትኩረት የተሰጠው የመራጮች ምዝገባ አፈጻጸም፣ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ሂደት፣ መደበኛ ተግባራትና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ሲሆኑ፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ውይይትና ግምገማ ተካሂዶ ለቀጣይ ግልጽ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
በግምገማው መሠረት የመራጮች ምዝገባ ሂደት ከታቀደው ደረጃ እንዳይደርስ ያደረጉ እንቅፋቶች ተለይተው በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ በመስጠት ውጤታማ አፈጻጸም ማሳካት እንደሚገባ ተገልጿል። በተለይም የአመራር ቁርጠኝነት፣ አቀናጅቶ መምራት እና የጊዜ አጠቃቀም በውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተጠቅሰዋል።
እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ ችግሮች በግልጽ ተለይተው በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሻሻል፣ በተጨማሪም “ዲጂታል ኢትዮጵያ” ራዕይን ለማሳካት ትኩረት ተሰጥተው እንዲሠራ ተጠይቋል። ይህም ሁሉንም ዜጎች ወደ ዘመናዊ አገልግሎቶች በእኩልነት ለማድረስ ያግዛል ተብሏል።
በአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ በመፍታት እና ሕዝቡን በንቁ ተሳትፎ በማሳተፍ አደረጃጀቶችን በቀበሌ ደረጃ ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል። ይህም የሥራ ቅንጅትን በማጠናከር ለቀጣይ ሀገራዊ ምርጫ ሂደት ውጤታማ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
ከመድረኩ የተነሱ ዋና ሐሳቦች መካከል አመራሩ ፈተናዎችን በማሸነፍ፣ የፓርቲና የመንግሥት ተልዕኮዎችን በታማኝነትና በብቃት በመፈጸም እስከ ታችኛው ደረጃ ድረስ ውጤት ማምጣት እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የአመራር ዋና ኃላፊነት መሆኑ በአንክሮ ተገልጿል።
በተጨማሪም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የሁሉም አካላት ተባብረው በኃላፊነት መሥራት እንደሚገባ በግልጽ ተጠናክሮ ተገልጿል። በመጨረሻም ሁሉም አካላት ተግባራቸውን በቅንጅት በመፈጸም ወደ ውጤት ማሻገር እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጦ መድረኩ ተጠናቀቋል።
ዘገባው፡ የማረቃ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።