22/05/2026
"ሰባተኛው ሃገራዊ ምርጫ ትላንትን የምናክምበትና ለነገ መሰረት የምንጥልበት ነው"ዲ/ን ተስፋው ባታብል
ላሊበላ፣ ግንቦት 14፣2018 (ላሊበላ ኮሙኒኬሽን) ብልጽግና ፓርቲ በላሊበላ ከተማ አስተዳደር የጎዳና ላይ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነርና በብልፅግና ፓርቲ የቡግና ምርጫ ክልል ፣ለክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት ዲ/ን ተስፋው ባታብልን ጨምሮ ሌሎች የዞንና የወረዳና የከተማ አስተዳደር የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም ዘርፍ የህዝቡን ክብርና ሉዓላዊነት የሚያስጠብቁ፣ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊትን የሚያረጋግጡና አፍሪካዊት ሃያል ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ዲ/ን ተስፋው ባታብል ተናግረዋል።
ሰባተኛው ሃገራዊ ምርጫ ትላንትን የምናክምበትና ለነገ መሰረት የምንጥልበት ነው ብለዋል ሃላፊው።
ምርጫው የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ የምናረጋግጥበት በመሆኑ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ታዓማኒነት ሁኖ እንዲጠናቀቅ የህዝቡ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ማሳያዎቹ በግብርና ዘርፍ የታየው ለውጥ መሆኑን ያነሱት ዲ/ን ተስፋው ባታብል ይህም የህዝቡ የጥረት ውጤት መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከዚህ ቀደም ከውጭ የምናስገባውን ስንዴ አሁን ላይ ራሳችን ለማምረት በቅተናል ያሉት ሃላፊው ይህ ስኬት የአርሶ አደሩ ድካም፣የመንግስት ድጋፍና የህዝብ ትብብር ውጤት ነውም ብለዋል።
7ኛው ሃገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ምዕራፍ የምንወስንበትና የወደፊት አቅጣጫችን የምንወስንበት ወቅት መሆኑን ነው ያነሱት።
ምርጫው በጥላቻና መከፋፈል አለያም በመደመርና በአንድነት መንገድ መጓዝ እንዳለብን የምንወስንበት በመሆኑ ዛሬ የምንሰጠው ድምፅ የቀጠዩን ትውልድ ህይወት ይወስናል ብለዋል።
ምርጫችን የስሜት ሳይሆን፣የሃገር ፍቅርና፣የሰላም ፍላጎትና የልማት አስተሳሰብ መሆን እንዳለበትም ነው ያስረዱት።
ፓርቲው መሰረቱ መደመር በመሆኑ አንዱ ሌላውን ማጥፋት ሳይሆን አብሮ መኖርና ለሃገር ጥቅም በጋራ መቆም በመሆኑ ብልፅግናን እንዲመረጡ ነው የጠየቁት።
የአማራ ክልል የገጠር መንገድ ኤጀንሲ አማካሪና በብልፅግና ፓርቲ በቡግና ምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪው ሙሉጌታ ገብረ ማርያም ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት አመታት በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ነው ያሉት።
ፓርቲው የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ፣ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና በቱሪዝም ልማት ዘርፍ በሰራው ስራ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ነው ያነሱት።
ፓርቲው ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማማ ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝ በማስታወስ ፓርቲውን በመመረጥ የተጀመሩ፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ምርጫው ሰለማዊ፣ፍትሃዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማህበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ነው የጠየቁት።
ብልፅግና ፓርቲ ሰው ተኮር መሆኑን ያነሱት የላሊበላ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሃላፊና የክልል ምክርቤት ዕጩ ተወዳዳሪዋ ዮርዳኖስ መርሻ ናቸው።
የሃገራችን የማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞ ለማስቀጠልና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ዳር ለማድረስ ብልፅግናን እንዲመርጡ ነው የጠየቁት።