15/08/2026
ክቡር አምባሳደር ዳባ ደበሌ በአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከጃፓን ገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊ ጋር ተወያዩ፡፡
ክቡር አምባሳደር ዳበ ደበሌ የጃፓን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የገዢው ፓርቲ - ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የዓለም አቀፍ ቢሮ ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት ክቡር ኮኖ ታሮ ጽ/ቤት በመገኘት ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም በቅድሚያ ስለኢትዮጵያ እና የጃፓን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ በአገራችን ስላለው ሰፊ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድል፣ ትኩረት ስለተሰጣቸው ኢንቨስትመንት መስኮች፣ ስለጃፓን ባለሃብቶች ተሳትፎ እንዲሁም በሪፎርም እየታገዘ በአገራችን እየተካሄደ ስላለው አስደናቂ የልማት እንቅስቃሴ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በመቀጠል ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ፣ ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ በምትገኝበት በዚህ ወቅት የአገር ውስጥ እና የውጭ የጥፋት ሃይሎች ጦር በመምዘዝ የአገሪቱን ልማትና የቀጠለውን ዕድገትና ብልጽግና ለማደናቀፍና ቀጣናውን ለማናጋት እያሴሩ እንደሆነና ለዚሁም ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ለማወቅ እንደተቻለ እንዲሁም ኢትዮጵያ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያደረገች ስላለው ጥረትና ስለያዘችው አቋም ለዳይሬክተር ጄኔራሉ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
እነዚህ ጸረ-ሰላም ሃይሎች ግንባር በመፍጠር እየፈጹሙት ያለው እኩይ ተግባር ለኢትዮጵያ ብሎም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ መሆኑን ያስገነዘቡት ክቡር አምባሳደር ዳባ ደበሌ የጃፓን የመንግስት ሁኔታውንና የአገራችንን አቋም ተገንዝቦ ጸረ-ሰላም እንቅስቃሴውን እንዲያወግዝ ጠይቀዋል፡፡
ዳይሬክተር ጄኔራሉ በበኩላቸው በቀጣናው የሚስተዋሉት ውጥረቶች በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸውና ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሄ ማስገኘት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሞው፣ ጃፓን ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡