06/09/2026
በኦማን የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ተመሠረተ
=====
(ሪያድ፣ ጳጉሜ 1 ቀን 208 ዓ.ም) በኦማን ሱልጣኔት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብት፣ ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲሁም ህብረታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል የኮሚኒቲ ማህበር በሙስካት ተመሠረተ።
በምስረታው ላይ የተገኙት በሳዑዲ አረቢያና በኦማን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር፣ መንግሥት ለዜጋ-ተኮር ዲፕሎማሲ የሰጠውን ትኩረት መሠረት በማድረግ ከማህበረሰቡ አባላት ጋር በአገልግሎት አሰጣጥና በዜጎች መብት ማስጠበቅ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደሩ በውይይቱ ወቅት ማህበሩ ከኢትዮጵያ ኤምባሲና ከኦማን የሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከልና ጠንካራ ድልድይ ለመሆን ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል። አክለውም ዜጎች ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ ተጠንቅቀው በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል። አምባሳደሩ የዜጎችን ህጋዊ የሥራ ዕድልና መብት ለማስከበር የቤት ሠራተኞችን፣ የሰለጠኑና ከፊል የሰለጠኑ ሙያተኞችን የሚያካትት የሥራ ስምሪት ስምምነት መንግስታችን ከኦማን መንግሥት ጋር ለመፈራረም የመጨረሻ መግባባት ላይ መድረሱንም አብስረዋል።
በታሪካዊው የምስረታ መድረክ ላይ የተሳተፉት የኦማን ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰቡን የሚያገለግሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን በነጻነት መርጠዋል።
በምስረታው በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚሲዮኑ ምክትል መሪ አምባሳደር አወል ወግሪስ ሙሃመድ እንዲሁም የቆንስላና የዳያስፖራ ጉዳዮች ኃላፊዎች ተገኝተው ኤምባሲው ለኮሚኒቲው አስፈላጊውን ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም፣ በኦማን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በቅርብ አገልግሎት የሚሰጥ ሚሲዮን በቅርብ ጊዜ ለመክፈት የሚያስችል አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ አምባሳደሩ አብስረዋል።